የሞርጌጅ ነገር!

የሞርጌጅ ነገር!

አንዴ እንዲህ ሆነ። ጊዜው 1997/98 አከባቢ ነው። የሞርጌጅ አሰራር ሕጉ ከሚያዘው በጣሙን ያፈነገጠ መሆኑን በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት ዳኝነት ስራዬ ጋር በተያያዘ ተገነዘብኩና አስራሩን ደረጃ በደረጃ ሕጉ ወደሚያዘው ማዕቀፍ ለመመለስ ያግዛል ብዬ ያሰብኩትን አንድ ፅሑፍ በ1996 ክረምት አዘጋጀሁ። ፅሑፉን “ዋስትና ያጣ የዋስትና ሕግ” የሚል ርዕስ ሰጠሁት። ዘለግ ያለ ፅሁፍ ነው፥ 83 ገፅ ያክላል። ፅሑፉን እንዲያይሉኝ በሞያቸው ለምተማመንባቸው ጥቂት ሰዎች አደልኩ። ፅሁፍን ካነበቡት መካከል አንዱ ወዳጄ “ፅሕፉስ ጥሩ ነው፥ ግን ይህን ያህል ገፅ የሚያንብልህ ስለማታገኝ በዘፈን መልክ ብታሳትመው ይሻልሃል” ሲል አስተያየቱን ሰጠኝ። አሽሙሩን ትቼ ቁምነገሩን ወሰድኩና ፅሑፉ የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፥ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና የፈደራል መጀመሪያ ፍርድ ቤት የወቅቱ ፕረዚዳንቶች አነበቡትና ተወያየንበት። ብዙ ካከራከረን በኋላ አሰራሩ ሕጉ ከሚለው ጋር የሚስማማ አይደለም የሚል ስምምነት ላይ ተደረሰ። አሰራሩ ለብዙ ጊዜ የቆየ በመሆኑ የኢኮኖሚ ቀውስ በማያስከትል መንገድ ቀስ በቀስ ሕጉ ወደሚያዘው አሰራር መመለሱ ተገቢ መሆኑ፥ ጠቀሜታውም ብዙ እንደሆነ (በተለይ ለተበዳሪውና ለሞርጌጅ አስያዡ) ተጠቅሶ ከሚመለከታቸው ግር ውይይት ቢደረግበት መልካም እንደሆነ አስተያየት ተሰጠ። በጥብቅና ስራ ላይ የነበሩ ጥቂት ሰዎችም ፅሑፉን አነበቡና እንዲሁ ተመሳሳይ አስተያየት ሰጡኝ።

ከዛ በኋላ የውይይቱ አድማስ ሰፍቶ የሁሉም ባንኮች ተወካዮች ባሉበት በራስ ሆቴል የግማሽ ቀን ስብሰባ ተደረጎ እኔ የፅሑፉን መሰረተ ሀሳብ አቅርቤ ውይይት ተካሄደ። ፅሑፉ በዋናነት የሞርጌጅ አሰራር ለባንኮች ያልተገባ ‘ስልጣን’ የሚሰጥ፥ የተበዳሪውና የዋሱ መብት እጅጉን የሚያጣብብ፥ የንብረት መብት አጠቃቀም ላይ ተገቢ ያልሆነ ገደብ በማድረግ ንብረትን የሚያመክንና የሀብት ብክነት የሚያስከትል መሆኑን የሚገልፅ ዝርዝር የያዘ ስለነበር ባንኮች ይወዱታል የሚል ግምት አልነበረኝም። እንደዛም ሆኖ ‘አሰራሩ የተለመደ ነው’ ከሚል አሰልቺ ክርክር ውጭ አሰራሩ ሕጉን የተከተለ ነው ወይም የፅሑፉ ይዘት ስህተት ነው በማለት የተከራከረ አልነበረም።

ከዛ በኋላ ግን ለካ ስብሰባው ላይ የሚረባ ክርክር ያላቀረቡት የንግድ ባንክ የሕግ ባላሙያዎች ፍርድ ቤቶች (በኔ መሪነት መሆኑ ነው) ባንኮችን ለማፍረስ እየሰሩ ነው የሚል ክስ ለአስፈፃሚው አካል አቅርበውና ፖለቲከኞቹን አሳምነው እዛ ሰፈር አቧራ አስነስተዋል። በዳኝነት ለቆየ ሰው የፖለቲከኞችና የሕግ ባለሟሎቻቸው ኩርፊያ የተለመደ ነው፥ ስለዚህ ብዙም ከቁብ አልቆጠርኩትም። ሰዎቹ ግን አምርረው ኖሮ የሕግ ማሻሻያ አቅርበው በፓርላማ ፀደቀላቸው። በፓርላማው የውይይት ሂደት በፍርድ ቤቶች ምክንያት ባንኮች ብዙ ኪሳራ እንደደረሰባቸው ተነገረ፥ ሌላም ብዙ ተባለ። አንዱም ግን እውነት አልነበረም።

ከዛ ወዲህ “ዋስትና ያጣው የዋስትና ሕግ” ብዙም ሳልገፋበት ቀረሁ። አሁንም ድረስ እጄ ላይ አለ። በወቅቱ አንድ አሳታሚ ጉዳዩን በወሬ ሰምቶ በመፅሐፍ መልክ ለማሳተም ፈቃዴን ጠይቆ ነበር። አልፈለግኩም።

የሞርጌጁ አሰራር ይኸው ለባንኮች እያደላ፥ ብዙዎችን ደግሞ እያስለቀሰ፥ በቢልዮን የሚቆጠር ንብረት ከገበያና ክኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውጭ እያደረገ ብዙ asset freeze እንዳደረገ አለ። ፕሮፌሰር ሬኔ ዴቪድ የፍትሀ ብሔር ሕጉ ሥራ ላይ ለመዋል ዓመታት እንደሚወስድበት ገልፀው ነበር፥ ሕጉ ከወጣ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ጥናት ያካሄዱት ፕሮፌሰር ቤክስትሮምም ይህን አረጋግጠው ነበር። ሁለቱም ሙሁራን ሕጉ ከ60 ዓመታት በኋላም ቢሆን ስራ ላይ መዋል እንደሚቸገር የገመቱ ግን አይመስለኝም። ለነገሩ ሞርጌጅን እንደምሳሌ አነሳሁት እንጂ ይህ ችግር በሌሎችም የሕግ ክፍሎች የሚታይ ነው።

ባንኮች በፈጠሩት አሰራር ምክንያት የኢትዮጵያ የዋስትና ሕግ የታለመለትን ዓላማ ማሳካት አቅቶታል። በመያዣ የተያዘን ንብረት ባንኮች ክሕጉ ዓላማ ውጭ በቁጥጥራቸው ስር እያስገቡ ሊሰጥ የሚችለውን የተሟላ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ እንዲያጣ አድርገውታል። እዚህ ላይ አንድ ምሳሌ ብቻ ልስጥ። 1,000,000 ብር የሚገመት ንብረት ለ50,000 ብር ዕዳ መያዣ ቢሆን ዕዳው ተከፍሎ እስኪያልቅ ድረስ ይኸው ንብረት አይሸጥም አይለወጥም። በዛው ባንክ ወይም በሌላ ባንክ ለሚሰጥ ሌላ ብድር መያዣነትም አያገለግልም። በሕጉ መሰረት ግን ሞርጌጅ real right (right in rem) ስለሆነ ንበረቱን ተከትሎ ይሄዳል እንጂ ሽያጭን አይከለክልም። ምርጫው የገዥው ነው፤ ለዕዳ መየዣ የሆነን ንብረት ለመግዛት የኢኮኖሚ አመክንዮ ካለው ሕግ እንቅፋት አይሆንበትም። አበዳሪው ንብረቱ ለዕዳ መያዣ መደረጉን ንብረት መዝገቡ ላይ እስካሰፈረ ድረስ ንብረቱ መሽጡ ወይም ለሌላ ብድር መያዣ መሆኑ ምንም ጉዳት አያደርስበትም።

አሁን ስራ ላይ ያለው የሞርጌጅ ውል አፈፃፀም ሰው ንብረት እያለው ድሀ እንዲሆን የሚያደርግ ነው። ብዙ ንብረት ከገበያ (circulation) ውጭ እንዲሆን በማድረግ በአጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይም አሉታዊ ተፅእኖ የሚያሳድር ነው። ስለዚህ አስራሩ መቀየሩ ለአገር (ለባንኮቹም ጭምር) የሚበጅ ነው። በመሆኑም በዚህ ዙርያ ዕውቀቱ፥ ልምዱ፡ ፍላጎቱ ያላቸው ሰዎች በጉዳዩ ላይ ቢገፉበት የብዙ ሰው አንባ ለማበስ ይረዳል እላለሁ።