በሚስት (በባልም) የጨከነው የውርስ ሕግ

በሚስት (በባልም) የጨከነው የውርስ ሕግ

ብዙ ሴቶች በውርስ ሙግት ሂደት ተስፋ ቆርጠው ሲያለቅሱ ማየት የተለመደ ነው። የኢትዮጵያ ሕግ ወራሽነትን በሚመለከት በወንድና ሴት መካከል ልዩነት አያደርግም። ሆኖም በብዙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች በውርስ ክርክር ሂደት ብዙ መንከራተት የሚደርስባቸው ሴቶች ናቸው። በኔ ዕምነት ለእንግልቱ ምክንያት የሆነው አንድም የሕጉ ጠማማነት፥ አሊያም በውርስ ማጣራት ሂደት የሚታይ ድክመት ነው።

የኢትዮጵያ የውርስ ሕግ በባልና ሚስት ላይ የወሰደው አቋም ጭካኔ የበዛበት ነው ቢባል ማጋነን አይደለም። የውርስ ሕጉ ሚስት ባልዋን (ባልም የሚስቱን) ከምትወርስ ንብረቱ ለመንግስት ገቢ ቢሆን ይመርጣል። ሚስት ከባልዋ ሀብት ምንም አትወርስም። ምንም! የባልየው ድርሻ ለሟቹ ልጆች፥ ካልሆነ ለወላጆች (ወይም ለልጆቻቸው)፥ ካልሆነ ለአያቶች (ወይም ተወላጆቻቸው)፥ ካልሆነ . . . . . ይተላለፋል ይልና ዘመድ አዝማድ ከሌለ ንብረቱ ለመንግስት ገቢ እንዲሆን ያዛል። የጋራ ንብረት ከነበረ ሚስት የራስዋን ድርሻ ብቻ ታገኛለች። የጋራ ንብረት ካልነበራት ግን የባሏ ሀብት ዓይኗ እያየ የሟቹ ልጆች ወይም ዘመዶች ይወስዱታል። በባሏ ሞት ምክንያት የደፈረሰው ህይወቷ በውርስ ሕግ ምክንያት ይበልጥ ይጨልማል። ብዙ ጊዜ ሴቶች የባል የኢኮኖሚ ጥገኞች በመሆናቸው ይህ ሁኔታ በህይወታቸው ላይ የሚፈጥረውን ምስቅልቅል መገመት ከባድ አይደለም። በሚስቱ ላይ ጥገኛ የነበረ ባል ሲኖርም ውጤቱ ተመሳሳይ ነው።

የባልና ሚስትን ወራሽነትን በሚመለከት የኢትዮጵያ ሕግ የወሰደው ይህ አቋም ብዙ አገሮች ከወሰዱት አቋም ይለያል። ብዙ አገሮች ይብዛም ይነስም ሚስት ባልዋን (ባልም ሚስቱን) እንድትወርስ (forced heirship) ይፈቅዳሉ። ከባልየው ንብረት ሲሶም፥ ሩብም ፥ ግማሽም፥ ሙሉውም እያሉ እንደየአገሩ ምርጫ ሚስት ከባልዋ የውርስ ንብረት ድርሻ እንዲኖራት፥ አንዳንዴም ከአንዳንድ ዘመዶች የውርስ ቅድሚያ እንድታገኝ በማድረግ ለትዳር ግኑኝነት ያላቸውን ክብር ያሳያሉ። አንዳንድ አገሮችማ በህይወት እስካለች ድረስ በጋራው ንብረት እየተጠቀመች እንድትቆይ (usufruct right) በመፍቀድ ከለመደችው የጋራ መኖርያ እንዳትፈናቀል ያደርጋሉ። ይህን በማድረግ ሞት ካስከተለው ሀዘንና ሰቆቃ በተጨማሪ በውርስ ክፍፍል ምክንያት ሌሌላ ተጨማሪ ውጣ ውረድ እንዳትጋለጥ ያግዛሉ።

በህይወት ዘመን ፍቅሩንም መከራውንም የምትጋራው ሚስት ከባል ሞት በኋላ ከሁሉም የራቀች ሆና እንድትቆጠር መደረጉ በቂ አመክንዮ ያለው አይመስልም። ሁለት ሰዎች በትዳር ከተጣመሩ በኋላ አንዱ ለሌላው ከሱ በላይ የቀረበ የለም። ስለዚህ ሚስት ከባሏ የውርስ ሀብት የተወሰነ ድርሻ የምታገኝበት፥ ቢያንስ ቢያንስ ግን ከሟቹ ወላጆች እኩል ወራሽ የምትሆንበት የሕግ ማሻሻያ ቢደረግ ይጠቅማል ባይ ነኝ። ይህ እንግዲህ የሕግ ማሻሻያ የሚጠይቅ፥ ብዙ ጊዜም ሊወስድ የሚችል ጉዳይ ጉዳይ ነው።

እስከዛድረስ ያለው አማራጭ በህይወት ያለው ተጋቢ እንዳስፈላጊነቱ ከሟቹ ንብረት ድጋፍ (ጡረታ/መጦርያ/ support/maintenance) እንዲያገኝ በማድረግ በትዳር ጊዜ የነበረው የመደጋገፍ ግዴታ በሞት ምክንያት እንዳይቋረጥ የሚያደርገውን የሕግ ማዕቀፍ መጠቀም ነው። ከላይ እንደተገለፀው ባል ወይ ሚስት አንዱ ሌላውን አይወርስም። ሆኖም ሕጉ በህይወት የቀረው ተጋቢ ለኑሮው አስፈላጊ የሆነውን ያህል ከሟች ሀብት ድጋፍ የማግኘት መብት ይሰጠዋል። በመሆኑም የግል ንብረት ያለው ባል ምንም ንብረት የሌላት ሚስት ትቶ ቢሞት ሚስት ሌላ ባል እስካላገባች ድረስ ከባልየው ንብረት የመጦር መብት አላት። ባልም እንዲሁ። ሕጉ ለሚስት (ወይም ለባል) የሚደረግ ድጋፍ ቅድሚያ እንደሚሰጠው የውርስ እዳ አድርጎ ይቆጠረዋል። በመሆኑም የሟች የሕግም ሆኑ የኑዛዜ ወራሾች የውርስ ተጠቃሚ መሆን የሚችሉት ከውርሱ ሀብት ለቀሪው ተጋቢ (ልጆችም ይሰራል) ኑሮ መደጎሚያ ቢቂ የሆነው ያህል ከተቀነሰ በኋላ ነው። የሟች ንብረት በቂ ካልሆነ ቅድሚያ የሚሰጠው ለመጦርያ (support/ maintenance) ስለሆነ ወራሾች ምንም አያገኙም።

የሚገርመው ነገር ይህን የመጦር መብት በኑዛዜ ወይም በሌላ መንገድ እንኳን ማስቀረት አይቻልም። ስለዚህ አንድ ወራሽ ከውርስ እንኳን ቢነቀል የድጋፍ መብቱ ቀሪ አይሆንበትም። ይህም ሕጉ በዚህ በኩል ያለውን ጥቅም ለመጠበቅ የሄደበትን ርቀት የሚያሳይ ነው። ይህ አሰራር በሞት ጊዜ ሊደርስ የሚችለውን የኢኮኖሚ መመሰቃቀል ሊቀርፍ ይችል ነበር። ሆኖም እንደሌሎች ብዙ የሕግ ጉዳዮች ይህም የሕግ ማዕቀፍ በውርስ ማጣረት ሂደት ብዙ ተግባራዊ አይደረግም። የዚህ ሕግ ተግባራዊ አለመሆን ገፈት ቀማሾች ደግሞ በዋናነት ሴቶች ናቸው።

በጥቅሉ የውርስ ሕጋችን ለተጋቢዎች የመውረስ መብት አይሰጥም። ይህን ለማካካስ ይረዳ የነበረው የመጦር መብትም ኑዛዜ በመስጠት መብት (freedom of testation) ተሸፍኖ ጠቀሜታው እስከዚህም ሆኗል። ይህ የሕግ እና/ወይም የአፈፃፀም ክፍተት በተጨባጭ ለሚታዩ ትላልቅ ችግሮች ምክንያት ሆኖ ይታያል። ስለዚህ ግትር የሆነውን ሕጋችንን ማሻሻል፥ እስከዛው ግን ከሟች ሀብት የመደገፍ መብትን ተግባራዊ የሚያደርግ የውርስ ማጣራት ስርዓት ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል።